Yene Shibet
Perspective

የእኔ ሽበት – ምነው አልነጋ አለ ለሊቱ እድሜ ገዛ ፥ ጭለማው አገር ላይ አለመጠን በዛ፥፥

የወለላዬ ወለሎታት – –

የእኔ ሽበት – የግጥም መድብል ቅኝት

ሰለሞን ሐለፎም

ወለሎ በኦሮምኛ ግጥም ማለት ነው። ወለሎታት የሚለውን ቅርጽ የሰጠው ዕውቁ የስነ ጽሁፍ ሰው ሰለሞን ዴሬሳ ነው። ሰለሞን ከዚህ አለም ከተለየ ብዙም አልቆየም። በኑዛዜው መሰረት በድኑ እንደተቃጠለ የሰማነው ይኖርበት ከነበረው ከወደ አሜሪካ ነው። እንኳን የልቡ ሞላለት። አፈሩንም ገለባ ያድርግለት። “ዘበት እልፊቱ” በተሰኘው የግጥም መድበሉ ወለሎ በሚለው የኦሮምኛ ቃል ላይ የግዕዝን አብዢ በመጨመር ሁለቱን አዳቅሎ ወለሎታት የሚል ቅርጽ አስተዋወቀ። ድንቅ እሳቤ ነው። ኩሽን ከሴም ጋር ማዋሀድ፣ ለነገሩ ከስነ ጽሑፉ በፊት ደማችን ተዋህዶ የለ። እንዲህ አይነቱን ቋንቋዎችን የማዳቀል ጥበብ መሬቱ ይቅለላቸውና በአንጋፋዎቹ በፀጋዬ ገብረ መድህን፣ በገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ በኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው)ወዘተ. ስራዎች ላይም አይተናል። አሁን አሁን ግን ከማስታረቅ ይልቅ ማጣላት የሚቀናው አንዳንድ የጎለደፈ ብዕር ስናይ አንጀታችን ድብን ብሎ መቃብር የወረዱትን ጎምቱ የስነ ጽሑፍ ልሂቃን መናፈቃችን አልቀረም።

አካሄዴ የግጥም አድባር ስለሰገደችለት አንድ ገጣሚ ትንሽ ለማለት ነው። ማትያስ ከተማ (ወለላዬ) ይባላል። ከብዕሩ ግጥም ይታለባል። በወረቀት ማሳ ላይ እንደ ገብስ ቆሎ የሚያማምሩ ኢትዮጵያዊኛ ፊደሎችን አሳምሮ ይዘራና ምን የመሰለ ጣት አስቆርጣሚ ግጥም ጀባ ይለናል – ለህሊናችን። ወለላዬ ወለልቱ ነው።

ወለልቱ በኦሮምኛ ገጣሚ ማለት ነው። እንደ መስቀል ወፍ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ብቅ የሚል ተራ ወለልቱ ሳይሆን የሁለለት ገጣሚ ነው። ብዕሩ ቀለም ጨርሶ አይነጥፍም። ነጋ ነጋ እንደምትታለብ ጥገት ላም ወተታዊ ሀሳብ ያንዶለዱላል እንጅ። ጭብጡ ቀላል፣ ቋንቋው ወላንሳ ነው። በቀን ተቀን ውሏችን ልብ ያላልናቸውን አጠገባዊ ጉዳዮቻችንን በገጣሚ ምናቡ ጨልፎና አጣፍጦ እንካችሁ ይለናል።ረቡዕ በነጋ ቁጥር በተከታታይ ለሁለት ዓመት ተኩል በላይ ያስኮመኮመን የረቡዕ ስንኞቹ ለዚህ ዋቢ ናቸው። የረቡዕ ግጥሞቹ አጥር ምጥን ያሉ ውስጣቸው ተፈልቅቆ የሚበላ ጣፋጭ ፍሬ አይነቶች ናቸው።

ሀሳቡ ደግሞ አለማለቁ! ስለምን ልጻፍ ብሎ አይጨነቅም። ስለሁሉም ነገር መጻፍ ይችላል። ልክ የማውራት ያህል ቀላል ነው ለእሱ። እንደ አንዳንዶቻችን ቃላት አምጦ አይወልድም። ስንኞቹ አልሰናኝ ብለውት አይፋጠጥም። እጇን ሳት ሳይላት የሰማው ምጣዷ ላይ ሊጧን አሳምራ እንደምታሰፋ ባለሙያ ጋጋሪ፣ ያለ ሀሳብ አስፍቶ ምን የመሰለ የግጥም እንጀራ ጋግሮ ማብላት ያውቅበታል። ረቡዕ በመጣ ቁጥር የወለላዬን የረቡዕ እንጎቻዊ ወለሎ ለማንበብ የምንናፍቅ የትየለሌ ነን። የወለላዬ የረቡዕ ወለሎታት እንደ ወለላ ማር ባንዳፍታ ዋጥ ስልቅጥ የሚደረጉ ናቸው። አላምጡኝ ፣ አፍ ውስጥ አገላብጡኝ አይሉም።

በቅርቡ ለንባብ ያበቃውን “የኔ ሽበት” የተባለ የግጥም መጽሐፉን በወፍ በረር ልቃኝና ስለ ወለላዬ አገጣጠም ስልት ስንጥር ሀሳብ ልሰንዝር። “የኔ ሽበት” ከስንኞች ምጣኔ አንጻር አብዛኞቹ ግጥሞች በወል ቤት ምጣኔ የቀረቡ ናቸው። የወል ቤት መነሻ እና መድረሻ ሁለት ሀረጎችን በያዙ ስንኞች የሚገነባ ነው። ለምሣሌ ያህል “አልሞተም አትበሉኝ”፣ “ሁሉም ጣዕሙን አጣ” እና “የስደተኛ ሕልም” የተሰኙትን መጥቀስ ይቻላል። አብዛኞቹ በዚህ ምጣኔ ይቅረቡ እንጅ አልፎ አልፎ የቡሄ በሉ በተሰኘው ምጣኔ የቀረቡ አንዳንድ ስንኞችም አሉ። ለምሳሌ ያህል “ነጋ ደግሞ ስራ ልግባ”፣ ” ገድለህ ማረው” እና “ አንተስ…?” በሚሉት ግጥሞች ላይ የተካተቱት አይነት ማለት ነው።

በአገጠጣም ስልቱ በልጅነታችን ያጣጣምነውን የከበደ ሚካኤልን ግጥሞች የሚመስሉ ተካትተውበታል። በንጉሡ ዘመን የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ሳለን አማርኛ በተማርንባቸው በከበደ ሚካኤል “ታሪክና ምሣሌ” መጻሕፍት ውስጥ የተካተቱትን እንደ“አዝማሪና የውሃ ሙላት”፣“የብረት ድስትና የሸክላ ድስት”፣ ” የዱባ ፍሬና የሾላ ፍሬ” ወዘተ የመሳሰሉትን ግጥሞች ዛሬም ድረስ የምናስታውሳቸው በአገላለጽ ለዛቸው፣ በቃላት መረጣቸው፣ በሁለለታዊ ጉዳያቸው ወዘተ ነው።

በ “የኔ ሽበት” የግጥም መድበል ላይም ሆነ በ ድረ ገጽ ጋዜጦች ላይ የወጡት የወለላዬ ግጥሞች በቀላል ዘወትራዊ ቃላት የተገነቡ በመሆኑ መልዕክቱ ለአብዛኛው አንባቢ ያለችግር ይደርሳል። ቅኔአዊነት የሌለባቸው ናቸው። ገጣሚ ከባድ ፈተና አውጥቶ ተማሪ እንደሚያስጨንቅ መምህር መሆን የለበትም። አላማው የእሱን ዕውቀት ማሳየት ባለመሆኑ በመራጃ እንኳን ሊፈነከቱ የማይችሉ ጠጣር ድንጋያማ ቃላትን እያጎረ ተደራሲ ላይ መታበይ የገጣሚ አላማ መአሆን የለበትም። ወለላዬ ከዚህ ነጻ ነው። ሳንመራመር አብዛኞቹን ግጥሞች ባንድ ጊዜ ነበባ ስለምን እንደሚያወሩ ማወቅ እንችላለን። እዚህ ላይ ከበደ ሚካኤልን ተኩ ከምንላቸው ግጥም ጸሐፊዎች መካከል አንዱ ወለላዬ ሆኖ እናገኛዋለን።

ከዚህ በተጨማሪ በግጥሞቹ ውስጥ ፈሰስ ብሎ የሚወርድ ትርክት አለ። በአንደበት የሚተረክ ወይም በስድ ጽሁፍ የሚቀርብን አቋማጭ ወግ በስንኞች የማቅረብ ያህል ነው። እንደ ዱላ ቅብብል አንዱ ስንኝ ለሌላው እያቀበለ ታሪክ ወደ እኛ ይፈስሳል – እንደ ቦይ ውሃ፡፡ “ጎሽ! እኔ አይደለሁም!፣ “በደንቡ ይመርመር”፣ “ሣርና ቅጠሉ” ፣ “መርቃችሁ ዝጉት” “ያላደላት አድባር”፣ “ሐዳስ ገብረዋህድ” እና “ገብርዬን አቃብሩኝ” ወዘተ. የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።

አንደበታዊው ወይም ስድ ጽሁፋዊው ለብዙው ሰው የተለመደ እና ቀና ሲሆን ግጥማዊው አቀራረብ ግን ችሎታን፣ ልምድን ይጠይቃል፡፡

ለምሳሌ ያህል “ፋኖስና ብርጭቆው” የተሰኘውን የከበደ ሚካኤል ግጥም ለአብነት ያህል ወስደን እንመልከት።

አንድ የፋኖስ መብራት በግብሩ የኮራ

እንዲህ ሲል ተጣላ ከብርጭቆው ጋራ

እኔ ነኝ መብራቱ ብርሃን የምሰጥ

ጨለማን አጥፍቼ የምገላልጥ

አንተ ግን እፊቴ እንዲህ ተደንቅረህ

ዙሪያዬን ከበኸኝ እንዲያው ተገትረህ

አልገባኝም ከቶ የምትሰራው ሥራ

ብርሃኔ ሩቅ ደርሶ ደምቆ እንዳያበራ

ተሰራጭቶ በጣም እንዳይዘረጋ

አንተን ፈጠረብኝ መንገድ የምትዘጋ

ዕንቅፋት እየሆንህ ሥራዬን አታጥፋ

ገለል በል ከፊቴ ብርሃኔ ይስፋፋ

አገልግሎቴማ ከሆነብኝ ጥፋት

እውነትማ ላንተ ከሆንኩህ ዕንቅፋት

ልሂድልህ ብሎ ሲለቅለት ቦታ

ከጎን የነፈሰ የነፋስ ሽውታ

መጣና መብራቱን አጠፋው ባንዳፍታ

አጭር እየሆነ ተመልካችነቱ

መለየት አቅቶት ጥቅሙን ከጉዳቱ

እወቁኝ እወቁኝ እያለ ሲነሳ

ሰውም እንደዚሁ ያመጣል አበሳ

በኤዞፕ (እንሰሴ) ተረቶች ማብቂያ ላይ የተረቱ ዋና ጭብጥ በጥቂት አረፍተ ነገሮች እንደሚገለጸው ሁሉ በዚህ አይነት ግጥሞች መገባደጃ ላይ የግጥሙን አንኳር መልዕክት በጥቂት ስንኞች ማስቀመጥ የተለመደ ነው።

ከፍ ሲል በቀረበው ግጥም ላይ ያሉት የመጨረሻዎቹ አራቱ ስንኞች የመልዕክቱ ማንጠሪያዎች መሆናቸውን ልብ ይሏል። በከበደ ሚካኤል ስራዎች ላይ የእነ ኤዞፕ አሻራ እንደሚታይ ሁሉ በወለላዬ አንዳንድ ግጥሞችም ላይ የከበደ ሚካኤል አሻራ መታየቱ አልቀረም፡፡

“የእኔ ላብ ነበረ” የሚለው ግጥም ለዚህ እሳቤ ዋቢ ሊሆነን ይችላል።

ሽልማት ያገኘ አሸንፎ ዋና

ለቃለ መጠይቅ አንዴ ቀረበና

እንዴት ነው ያሸነፍክ የሆንከው አንደኛ?”

ብሎ ሲጠይቀው አንዱ ጋዜጠኛ

እገንዳው ገብቼ በልምምድ ሳመሽ

የእኔ ላብ ነበረ የውሃው አጋማሽ

ብሎ የመለሳት ያስቀመጣት ቃላት

መልዕክት የጨበጠ ፍሬ ነገር አላት

የሰው ልጅ ለአላማው ከደከመ ለፍቶ

መደሰቱ አይቀርም ያሻውን አግኝቶ

ቀደም ሲል እንዳየነው ሁሉ በዚህ የወለላዬ ግጥምም አራቱ መቋጫ ስንኞች ጭብጡን ተሸካሚ መሆናቸውን ልብ ይሏል።

በሌላ በኩል ወለላዬ ሰው እንደዘበት ያጫወተውን፣ በወሬ መካካል የሰማውን አንድ እፍኝ ጉዳይ አሰማምሮ በስንኞች ማቅረብ ያውቅበታል። ወይም ለባለሙያ ሴት አይደርቄ ጎመን እና በሶብላ ብቻ የመስጠት አይነት ነው። እሷ ቅመማ ቅመም ጨማምራና በወጉ አበሳስላ ስክን ያለ ማባያ ልትሰራ እንደምትችል ማለት ነው።

አንድ አፍሪካዊ ባልንጀራዬ እንዲህ ሲል አጫወተኝ። አንድ ቀን አመሻሽ ላይ ከስቶክሆልም ከተማ እንብርቶች መካከል ባንዱ ሲዘዋወር ከወደ አረብ ሀገር የመጣ አንድ ጎረምሳ ወደ እሱ ቀረብ እያለ መንገድ እንደመዝጋት ብሎ ብልጭልጭ ወርቅ መሳይ ነገር ዘርግቶ ትገዛለህ ብሎ ጠየቀው። ወደ ጉዳዩ የሚጣደፈው ጓደኛዬም በአልፈልግም አይነት ገለል በልልኝ ከዚህ ብሎ እጁን ሲያወናጭፍ በድርጊቱ የተናደደው አረብ “ኢቦላ!” ብሎ መሳደብ። በዚያን ጊዜ ይህ በሽታ በአፍሪካ አንዳንድ ሀገሮች ብዙ ሰው እየጨረሰ ነበር። በዚህ የተናደደው ጓደኛዬም“ አልቃይዳ!” በሚል ምላሽ አንጀቱን አርሶ ሄደ እላችኋለሁ፡፡

ለወለላዬ ይኸ ጥሬ መረጃ ነው። መረጃውን ቀባብቶና አሰማምሮ በስንኞች ሊያቀርበው አይሳነውም። እንደዘበት ከሰማው ወግ ላይ የመዘዘውን ሰበዝ ወግ፤ አክርማ፣ አለላ፣ ወንጋ ወዘተ ጨማምሮና አስጊጦ አሪፍ ጌጠኛ ግጥማዊ ወግ እንካችሁ ይለናል። ሌሎች ሰዎች የነገሩኝ ናቸው በሚል ያቀረባቸው “ደኅና ነኝ ኢ.ህ.አ.ፓ”፣ “የእንቁጣጣሽ ጠላ”፣ “ቀኝ አይኗ ነበሩ” እና ”ያነሱት የለም ወይ” የሚሉት እጥር ምጥን ያሉ አስፈጋጊ ግጥሞቹ ለዚህ ዋቢ ናቸው።

“ያነሱት የለም ወይ?” የሚለውን ግጥም እንመልከት፡፡

በላይ መረሳ የኮሜዲው አባት

ልጁ ግዳጅ ሊሄድ ተደግሶ ሽኝት

ሳቅ ጨዋታው ደምቆ ሲደነስ ሲጨፈር

ልጁ እደጅ ወጥቶ ከወዳጆቹ ጋር

የት ሄደ ብሎ ሲል በላይ ተቆጥቶ

ሊነሳ ነው ቢሉት ማስታወሻ ፎቶ፤

ምን ያስቸኩለዋል አየ የልጅ ነገር

ያነሱት የለም ወይ ሲሄድ ወደዛ አገር

ብሎ እንደቀለደ ልጅየው ነገረኝ

አንድ ቀን በድንገት ቡና ቤት አግኝቶኝ

“አልሞተም አትበሉኝ” የሚለው ረጅም ግጥም በቀዳሚው ዘመን ከምናውቃቸው ገድላዊ ግጥሞች ጋር በመጠኑ ይመሳሰላል። ብዙ ስንኞችን ያካተተ ረጅም ግጥም በጥንቃቄ ካልተሰናዳ የአንባቢን ስሜት ቆንጥጦ የማቆየት ሀይል ላይኖረው ይችላል። ይሰለችና ይቋረጣል። ይህ የወለላዬ ግጥም ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስመ ጥር የነበሩ ምውታን የሀገር መሪዎችን፣ የጦር አበጋዞችን፣ጋዜጠኞችን ወዘተ. እያዋዛ የዘከረበት ነው። እንዲህ ብዙ ሰዎችን ባንድ የግጥም ገበታ ውስጥ አካትቶ ማወደስ ካሁን በፊት የተለመደ ባለመሆኑ ምናልባት ወለላዬ የስልቱ ጠንሳሽ ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል።

ይህንን ካነሳን አይቀር መጠሪያ ስሞችን ብቻ በማቀናጀት ስንኞች አሰናኝቶ “ስምም ይጣላል ወይ?” በሚል ርዕስ ጀባ ያለን ግጥም በቃላት መጫወት እንደሚችል ማሳያ ሊሆን የሚችል ይመስለኛል።

ፀዳለና አፀደአስካለችፈለቀች

ብሬጌጤስንቄጉዳዬአሰገደች

ጥሩወርቅጌጃ ወርቅብርቱካንአዛለች

ሎሚናትትርንጎእቴነሽአበበች

የማታይርገዱአለሚቱአስናቀች

እያለ ይቀጥላል፡፡

እንደ ኳ፣ ቋ፣ጧ፣ የመሳሰሉትን መልዕክት አስተላላፊ የሆኑ ብቸኛ ፊደሎች ተጠቅሞ ያደራጀው ግጥምም እንዲሁ እኛ ልብ ያላልናቸውን ጥቃቅን ነገሮች በፈጣሪነት ችሎታው ተጠቅሞ ህልው እንደሚያደርጋቸው አመላካች ነው። ይህንን ማለቴ ነው፡፡

ብሎ ተናግሮ እያስጠነቀቀው

ብሎ ወደቀ መካሪን ሳይሰማው

ብሎ ፈረጠ ያበጠው አካሉ

ብሎ ፈሰሰ ደምና መግሉ

ብሎ ተከፍቶብሎ ፈነዳ

ብሎ ተሰብሮ አስታቀፈን እዳ

እያለ ይቀጥላል፡፡

ስድ ጽሑፍን ከግጥም ጋር አቀናጅቶ ማቅረብ በከበደ ሚካኤል ስራዎች ላይ አልፎ አልፎ ይታይ ነበር። ለምሳሌ ያህል በ”ታሪክና ምሳሌ” ላይ የቀረበውን የሚከተለውን በከፊል ወስደን እንመልከት፡፡

ስካሮን የሚባለው የፈረንሳይ ተወላጅ የሆነ ባለቅኔ ክፉ የቁርጥማት ደዌ አድሮበት የሚበልጠው እድሜውን ካልጋ ሳይነሳ ሲማቅቅ ኖሮ ከዚህ ሕመሙ ሳይፈወስ እንደ ታመመ ኖሮ ሞተ፡፡ ከመሞቱም በፊት ይህንን መከራውን የሚገልጥ ቃል በግጥም አድርጎ ጽፎ በሞትሁ ጊዜ በመቃብሬ ድንጋይ ላይ እንድትጽፉት ብሎ አደራ ሰጠ።

ሕይወቴን በሙሉ ዐልጋ ላይ ታስሬ

ታምሜ ስማቅቅ ስንገላታ ኖሬ

ሥቃዬን ጨርሼ ይኸው ዛሬ ገና

እንቅልፌን አግኝቼ ማረፌ ነውና

የምሄዱ በዚህ በመቃብር ቦታ

እንዳትቀሰቅሱኝ እለፉ በእርጋታ

ወለላዬም እንዲህ አይነት ቅይጥ ስራዎችን በመድበሉ ላይ አካትቷል።

“ያላደላት አድባር”፣ “መንግስቱ ገዳሙ”፣ “ፈጣሪ ሆይ! ይቅር በለን” በሚሉትና በሌሎቹም አንዳንድ ግጥሞቹ መነሻ ላይ መንደርደሪያ ሀሳብን ለተደራሲው አስቀድሞ በስድ ጽሁፍ መልክ በማቀበል የንባብ መንገዳችንን አቅልሎልናል።

እግረ መንገዳችንን አንድ ትንሽ ነገር ብለን የዛሬውን መጠነኛ ምልከታ እዚሁ ላይ እንደምድም። ግጥም ሁሉን አውሪ፣ ሁሉን ነጋሪ ባይሆን ይመረጣል። በጣቶቹ ቆርሶ፣ በጥርሶቹ አላምጦ መዋጥ ለሚችል ጤነኛ ዐዋቂ ሰው ፈትፍተን ማጉረስ አይጠበቅብንም። በእራሱ እጅ ሲበላ ነው የሚጠግበው።

“ብርሃን ፍለጋ” የሚለው የወለላዬ ግጥም እንዲህ ቀርቧል።

ምነው አልነጋ አለ ለሊቱ እድሜ ገዛ

ጭለማው አገር ላይ አለመጠን በዛ፡፡

በሩቅ የሚታየው ወጋገኑም ጠፋ

ምን ይሻለን ይሆን ይኸ ዘመን ከፋ

ብርሃን መቼ ነው ፈንጥቆ በአገር ላይ

እሰይ ነጋ ብለን ደስ ብሎን የምናይ?

መቼ ይሆን ነግቶ ጭለማው ተገፎ

ፀሐይን የምናይ ይሄ ዘመን አልፎ

አልነጋልን አለ እውነትም ሳይነጋ

በጭለማ አለቅን ብርሃን ፍለጋ

አራተኛውና አምስተኛው ስንኞች በብርሃን ፍለጋ ውስጥ ቦግ ብሎ የበራውን የግጥሙን ጧፍ ለማድከም በሚውተረተር ሽውታ ነፋስ ይመሰላሉ። የተሸፋፈነን ውበት እሱ ራሱ በእጁ ገላልጦ መዳበስ ለሚፈልግ ተመልካች እንካ ተመልከት ብሎ ገልጦ የማራቆት ያህል ነው። አንዳንድ ጊዜ ለተደራሲውም የቤት ስራ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ለዛሬው በዚሁ ይብቃን። ቸር እንሰንብት!!

 

 

ምንጭ:  Welelaye Weleaye የፌስቡክ ገጽ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *