*ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ*
የዜጎች ጤና እንዲጠበቅ ሐኪሞች፣ ነርሶች፣ የጤና መኮንኖች፣ ድሬሰሮች፣ የላብቴክኒሽያኖችና ሌሎችም የጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች በልተውና ጠጥተው፣ መጠለያና ሌሎችም ፍላጎቶቻቸው ተሟልተውላቸው ለመኖር መቻል አለባቸው።
በጦርነት ኢኮኖሚ እየደቀቀች ባለች ሀገር ዉስጥ ሠላም ከመታጣቱና ፀጥታም በበርካታ የሀገራችን ክፍሎች ከመበላሸቱ በተጨማሪ የኑሮ ውድነቱ እጅግ ከባድ ሆኗል።
ዜጎች በተለይም የወር ደሞዝተኞች በሀገራችን ውስጥ ከሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት ጋር የሚመጣጠን የደሞዝ ዕድገት በሌለበት ሁኔታ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን እና ግልጋሎቶችን ለመሸመት በማይታበል ደረጃ አቅቷቸዋል።
አስፈላጊ የሆኑትን ወጭዎቻቸውን ሸፍነው ለመኖር እንዲኖሩ ማስቻል ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው። ለዜጎች መስጠት ያለባቸውን ሙያዊ ግልጋሎት ሊያበረክቱ የሚችሉት የራሰቸውም ሁለንተናዊ ጤና ሲጠበቅ ነው።
ያለ በቂ ምግብ፣ ያለ በቂ ልብስ፣ ያለ በቂ መኖሪያ እነሱ እንዲኖሩ ማድረግ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አስፈላጊ የሆነውን አገግሎታቸውን ማበርከት እንዳይችሉ ማድረግ ነው። አገልግሎታቸውን የሚመጥን ገቢ ሊያገኙ ይገባቸዋል። የህክምና ባለሙያዎችንም ሆነ የሌሎች ባለሙያዎችን ይህንን ተገቢ ጥያቄ አለመመለስ የሁሉንም ዜጋ ጤና አደጋ ላይ እንደመጣል የሚቆጠር ስለሆነ ባፋጣኝ አጥጋቢ አዎንታዊ መልስ ሊሰጣቸው ይገባል።
የሚሰጠውን ግልጋሎት የሚመጥን ክፍያ መጠየቅ የማንም ዜጋ መብት ነውና መንግሥት ልክ የመምህራንኑን ጥያቄ በእመቃ “ለመፍታት” እንደሞከረው ያንኑ የለመደውን መንገድ እንዳይደግም እንመክራለን።
የሚገባቸውን የአገልግሎታቸውን ዋጋ ጠየቁ እንጂ ከሀገሪቱ አቅም በላይ አድርጉልን አላሉም። ለነገሩ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በሙስና ከሚተዳደሩት የገዥው ፓርቲ አባላት በስተቀር የሁሉም ደሞዝተኞች ገቢያቸውና ለመኖር የሚያስፈጋቸው ወጭ እጅግ በጣም ተራርቋል።
ዛሬ መሰረታዊ የሚባሉትን ፍላጎቶች ለማሟላት አብዛኛው ዜጋ አቅም አጥቷል። ፍላጎትን በደመወዝ ብቻ አሟልቶ መኖር ቅንጦት ግፋም ሲል ምኞት ሆኗል።
የኑሮ ውድነት የብዙሃኑን ሕይዎት እያናጋ ባለባት ሀገርና ሁኔታ ነው የሕክምና ባለሙያዎች የጭንቀት ድምጻቸውን በድጋሚ ለማሰማት የተገደዱት። የመሰረታዊ ፍጆታዎችና የሌሎችም ዕቃዎች ዋጋ ንረት እነሱን ብቻ ሳይሆን መላውን ህብረተሰቡ ከማማረር አልፎ በመኖር ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ እያደረጉትም ነው።
በኑሮ ውድነቱ ከሕክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ መምህራኑና ዝቅተኛ ደመወዝተኛ የሆኑት የመንግስት ሰራተኞች፣ ምንዳ የሚከፈላቸው የቀን ሰራተኞች በሙሉ ናቸው።
ቁጥር ስፍር የሌላቸው የሥራ አጦቹን የጉስቁልና ህይወት በዐይነ ኅሊና ማየቱም ተገቢ ነው። አዳዲስ የሥራ መስኮች እየተፈጠሩ ቢሆን ሥራ ፈላጊዎች በሀገራቸው ውስጥ ሰርተው ለመኖርና ህይወታቸውን ለማሻሻል በፈለጉ እና በቻሉ ነበር። ዛሬ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደሀገራችን የወንዝ ውሀ በሁሉም አቅጣጫ ሀገራቸውን ለቀው እየፈሰሱም፣ እየፈለሱም ናቸው።
ዜጎች በሠላማዊ መንገድ ተገቢ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ በአግባቡ ፈጥኖ ምላሽ መስጠት ደግሞ የመንግሥት ችሮታ ሳይሆን ግዴታው ነው።
የገዥ ፓርቲ፣ የገዥ መደብ፣ የገዥ ወገን፣ … የሆኑት ቀሪውን ዜጋ እንደ አገልጋያቸው ሊመለከቱት አይገባም። ሁሉም ዜጎች በክብር የመኖር መብት እንዳላቸው ለደቂቃም መረሳት የለበትም እንላለን።
ለቀለብ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለልጆች የትምህርት ቤት *ያውም ትምህርት ቤቶች አገልግሎት በሚሰጡባቸው ከባቢዎች*፣ ለህክምና፣ ለመጓጓዣ፣ ለመብራትና ለወሀ፣ … የሚደረጉት ክፍያዎችና ሰራተኞች የሚያገኙት የወር ገቢ ካልተመጣጠኑ ኑሮ ቧገታ ነው የሚሆነው።
የእያንዳንዱ የፍጆታ ዕቃ ዋጋ በየዕለቱ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም። ያለጥርጥር በብዙ አምራች አካባቢዎች ሠላምና ጸጥታ በመጥፋቱና አምራች ዜጎችም በቂ ግብአቶችን አገኝተው ለማምረት የሚችሉበት ሁኔታ ባለመኖሩ የምርት እጥረት አመርቃዥ ችግር ሆኗል።
ችግሩ እየከፋ መጥቶ መንግስትም ጆሮ ዳባ ልበስ በማለቱ የችግሩ ሰለባዎች ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሰዋል ለማለት ባይቻልም በየወቅቱ የሚሰሙት ጉምጉምታዎች ወደ ቁጣ እስከሚለውጡ መጠበቅ ትክክል አይሆንም።
በአሁኑ ሰዓት በሠላማዊ መንገድ ከፍተኛ ግን እጅግ ተገቢ የሆነ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉትን የሕክምና ባለሙያዎችን ጥያቄ መንግሥት ፈጥኖ በአግባቡ ሊመልስ ይገባል። የመምህራኑም ሆነ የቀሩት ሠራተኞች ጥይቄ የተዳፈነ እሳት ነውና ሊንቦገቦግና እንደሰደድ እሳት ሊዛመትም ይችላል። መንግስት ቢያንስ ማኅበራዊ ሠላምን ለማምጣት ባይችል እንኳን እነዚህን ሰላማዊ እና ተገቢ ጥያቄዎች ለማፈን ግን በፍጹም እንዳይሞክር እንመክራለን። ዘንድሮ አምና አይደለምና!!
የጤና ባለሙያዎች ለረጅም ጊዜ በትምህርት ቆይተውና ጠቃሚም ዕውቀትን ገብይተው ቀሪ ዘመናቸውን የሚያሳልፉት ደግሞ የታመሙ፣ የተጨነቁ፣የሚሰቃዩ፣ ተስፋቸውን በሀኪሞችና በፈጣሪያቸው ላይ በጣሉ ህሙማን ታካሚዎችና አስታማሚዎች ተከበው ሁሌም ዐይን ዐይናቸውን እየተመለከቷቸው፣ ዜጎችን ከሞትና ከስቃይ ለማዳን በመትጋት ነው።
ዛሬ እነዚህ ባለሙያዎች ችግራችንን ፍቱልን ሲሉ በቅንነትና በፍጥነት ሊደመጡ ይገባል። ሁሉም ዜጋ ያለምንም መወላወል ለዶክተሮቻችን ድጋፉን፣ ያልተሸራረፈ ወገንተኛነቱን ሊያሳያቸው ይገባል።
ከድህነት የተነሳ ታካሚዎች የመድሐኒት መግዣ ገንዘብ አጠረን ሲሏቸው፣ አብረው ይጨነቃሉ። እንደ አለመታደል ሁኖ እነሱም በችግር ላይ ስለሆኑ ካላቸው ስለማካፈል ማሰብ አይችሉም።
የጤና ችግራቸው ደም በመለገስ የሚፈታ ከሆነ ባልበላና ባልጠጣ ጎናቸው ተንጋለው ተኝተው ደማቸውን ሲለግሱ በከፍተኛ የሃላፊነትና የወገንተኝነት መንፈስ ነው።
የህክምና ባለሙያዎች <ሥራችንን የሚመጥን ደመ-ወዝ አልተከፈለንም፣ ደሞዛችን በጣም ዝቅተኛ ነው፣ የተለዩ ጥቅማጥቅሞች በዓለም ጤና ጥበቃ /WHO/ ዕሳቤ ሊከፈለን በተገባ ነበር > ነው እያሉ ያሉት።
ለዜጎች ጤናና ህይወት ወሳኝ የሆነውን ሙያዊ ስራቸውን እየሠሩ በሠላማዊ መንገድ ነው ድምጻቸውን በጋራ እያሰሙ ያሉት። ሁሉ በእጄ ሁሉም በደጄ የሚሉት ባለሥልጣናትና ካድሬዎቻቸው አንገብጋቢ የሆነን የሀኪሞች ጥይቄ ለማድበስበስና እነሱንም ለማዘናጋትና የሚያደርጉት ሙከራ በፍጹም አይጠቅምም እንላለን።
መብትንና ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚደረግ የሙያተኞችና የሠራተኛው መደብ አባላይ ትግል በአፈናና በመሸዋወድ አይፈታም። በቅንነት ለቀረበ ተገቢ ጥያቄ ተገቢው አዎንታዊ ምላሽ ያስፈልገዋል።
ዛሬ የሐኪሞች ጥያቄ ጎልቶ ቢወጣም፣ የሌሎች ሙያተኞችና የሠራተኛው ህዝብ ጥያቄዎች ታፍነው እየተብላሉ መቆየታቸውን መዘንጋት አይገባም።
ትግላቸውን መንገድ ለማሳት <ህዝብን ለማገልገል ቃለ-መሓላ ገብታችሁ ነው የምትሠሩት ማለትም ሆነ፣ የቤት መስሪያ ቦታ ይሰጣችኋል፣ ከባንኮች ጋርም በመነጋገር ብድር እንድታገኙ እያመቻቸን ነው፣ … > ብለው ለማዘናጋት መሞከር መፍሄ አያመጣም።
እውነታው ግን ቃለ-መሐላ የተገባው በፍትሀዊነት በቅንነት በታዛዥነት ለማገልገል ነው እንጅ ሊያኖር በማይችል ደመወዝ እና የኑሮ ሁኔታ እየተቸገሩ ለማገልገል አይደለም!!!
ገዥዎች ቃላቸውን በማይጠብቁበት ሀገርና ሁኔታ ሐኪሞቹን ስለገቡት ቃል ኪዳን ማንሳትስ ምን ይባላል?!?! የሀገሪቱን ወጣት ዜጋና ሀብት በራሱ ህዝብ ላይ በሚያካሂደው ጦርነት ውስጥ ሳይሳሳ የሚማግድ መንግሥት የጤና ባለሙያዎች እየተራቡና እየታረዙ፣ የሰው በክብር ራሱን ችሎ ለመኖር ከሚያስፈልገው በታች ለመስራትና የቧገታ ህይወትን እንዲመሩ ማስገደድ አልያም ማታለል አይችልም።
“ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል” ነውና መንግስት ተገቢ የሆነውን ጆሮ ሰጥቶ ቀን የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄዎች ፈጥኖ ሊመልስ ይገባል ይላል – ኢሕአፓ!!!
በኑሮው እየተማረረ፣በበርካታ ጉዳዮችም እየተሰቃየና እየበገነ ያለን ባለሙያ የያዘ የጤና ስርዓትም ሆነ የትምህርት ተቋም፣ ይህንን ሁኔታ በቅርበት እያዩ የሚማሩ ተማሪዎችን የያዙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሀገርም ለወገንም ከሚያበረክቱት አስተዋጾ አስተማማኝ ሊሆን አይችልም። አስተምረው ለስደት፣ ለሀገር የሚያተርትፈው ውድቀትን ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ ተገቢ ጥያቄ ካቀረቡት የኢትዮጵያ ሀኪሞች ጎን ይቆማል።
የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ትክክለኛ የመብት ጥያቄ ነውና በፍጥነት ይመለስ እንላለን!!
ትግላችሁ ፍትሃዊ በመሆኑና በሠላማዊ መንገድ የቀረበም በመሆኑ ግቡን እስከሚመታ ከጎናችሁ እንቆማለን።
ኢሕአፓ ከተገፉትና መብታቸውን ለማስከበር ከሚታገሉት ወገኖቻችን ጋር ዛሬም እንደወትሮው በአንድነት ቆሞ እንደሚታገል ማረጋገጥ ይወዳል።
ሚያዝያ 30/8/2017
አዲስ አበባ