News

ኮሮናቫይረስ፡ የኢትዮጵያዊቷ የ’ማስክ’ ሥራ ጅማሮ

የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ሰው በሚሰበሰብባቸው ሥፍራዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ወይም በእንግሊዘኛው ማስክ ማድረግ ይመከራል።

Source: bbc.com/amharic

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት ጭምብል ማድረግን ግዴታ አድርገዋል። በመጓጓዣ፣ በመደብሮች እንዲሁም ሰው በሚበዛባቸው ሌሎች አካባቢዎችም ማስክ ማጥለቅ ራስን ከኮቪድ-19 ለመከላከል መደረግ ካለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች አንዱ ነው።

በመላው ዓለም ከ4.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል። በሽታው በስፋት መሰራጨቱ ጭምብልን በመላው ዓለም እጅግ ተፈላጊ ከሆኑ ቁሶች አንዱ አድርጎታል፤ ዋጋውም ንሯል።

አገራት ማስክ በብዛት ከማምረት ባሻገር፣ በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎች ወደ ጭምብል ምርት እንዲገቡም እየጠየቁ ነው። ከእነዚህ መካከል ዲዛይነሮችን መጥቀስ ይቻላል።

የህክምና ባለሙያዎች የሚጠቀሙት ኤን-95 እንዲሁም የሌሎች አይነት ማስኮችም እጥረት አለ። ስለዚህም በቤት ውስጥ የሚሠራ ጭምብል እንደ ሌላ አማራጭ ይወሰዳል።

የዲዛይነሮቹ ጅማሮ

ከ110 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሚኖሩባት ኢትዮጵያ ማስክ በበቂ ሁኔታ ማዳረስ ፈታኝ ይሆናል። ሰዎች በቤታቸው ማስክ ቢያዘጋጁ ወይም በተለያየ አይነት የልብስ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በብዛት አምርተው በተመጣጣኝ ዋጋ ቢያቀርቡ ጫናውን ያቀለዋል።

ይህንን ከግምት በማስገባት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ከእነዚህ አንዱ ደግሞ የዲዛይነር ማኅሌት አፈወርቅ (ማፊ) ጅማሮ ነው።

ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱን ተከትሎ፤ ከሁለት ወር በፊት ነበር ማስክ ወደማምረት የገባቸው። ያኔ ጥቂት ጭምብሎች ሠርታ ለሰፈሯ ሰዎች ሰጥታ ነበር።

ከዚያም በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ስር የተለያዩ የእርዳታ ቁሳቁሶች ሲሰባሰቡ ማስክ ለግሳለች። 500 ማስኮች ለታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶችም ሰጥታለች።

ዲዛይነሯ እስካሁን 2500 ጭምብሎች በእርዳታ የሰጠች ሲሆን፤ እስከ 10 ሺህ ጭምብሎች የመለገስ እቅድ እንዳላት ለቢቢሲ ተናግራለች።

አሁን የምርት መጠን ጨምራ ሥራ ማቆም ላልቻሉ፤ እንደ ባንክና ፋብሪካ ያሉ ተቋሞች ማከፋፈል ጀመራለች። ማስክ የምትሸጠው በ30 ብር ሲሆን፤ የጥበብ ዲዛይን ወይም የድርጅት አርማ ያላቸው ማስኮችም በተለያየ ዋጋ መቅረባቸውን ትናገራለች።

ማፊ ከሠራቻቸው ማስኮች ጥቂቱን ደጉማለችImage copyrightMAFI/TWITTER
አጭር የምስል መግለጫማፊ ከሠራቻቸው ማስኮች ጥቂቱን ደጉማለች

የምትሠራቸው ማስኮች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የተለያዩ አገሮችን ምርቶች የዳሰሳ ጥናት እንደሠራች ማኅሌት ትናገራለች። የቱ ጨርቅ ከየቱ ይበልጣል? በሚልም በተሻለ ጥራት ለማምረት ጥናት ማድረጓንም ታክላለች።

እንደማፊ ሁሉ ሌሎች ዲዛይነሮችም ወደ ማስክ ምርት እየገቡ ነው። ዲዛይነር ፍቅርተ አዲስ ከእነዚህ አንዷ ናት። የዊዝ ኪድስ መስራች ብሩክታዊት ጥጋቡም ‘ሽፎን ኢትዮጵያ’ የተሰኘ እንቅስቃሴ ጀምራለች።

ማፊ እንደምትለው፤ ፍቅርተን ጨምሮ ከሌሎች በፋሽን ዘርፍ ካሉ የሙያ አጋሮቿ ጋር በምን መንገድ ማስክ ማምረት እንደሚችሉ፣ መንግሥት ለጭምብል ምርት ጨረታ ቢያወጣ በምን መንገድ መሳለፍ እንዳለባቸውም ምክክር እያደረጉ ነው።

ማፊ ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ እሷ፣ ፍቅርተና ብሩክታዊት ከሳምንታት በፊት ከጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ጋር ተገናኝተው ነበር።

ለጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤቱ በምን መንገድ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ እንዲሁም የማስኮች የጥራት ደረጃ ምን ይምሰል? በሚለው ላይ ውይይት እንዳደረጉ ዲዛይነሯ ትናገራለች።

የሚሠሩበት ቦታ ተጎብኝቶ ፍቃድ እንደሚሰጣቸው ከጤና ሚንስተሯ ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተረዱም ገልጻለች።

የማምረቻ ቦታ ንፅህና፣ ሠራተኞች ጓንትና ጭምብል ማድረጋቸው፣ ጭምብሉ የሚታሸግበት ቦታ ንፅህና፣ ምክር የሚሰጥ የጤና ባለሙያ መኖሩ በደረጃ ግምገማ ወቅት ከግምት የሚገቡ መስፈርቶች ናቸው።

ከሳምንታት በፊት የወጣ መመሪያ የጨርቅ ማስክ ሲሠራ በሁለት ድርብ መሠራት እንዳለበት ተጠቁሟል።

ማፊ በኢትዮጵያ ያለው የማስክ ፍላጎትና የአምራቾች ቁጥር እንደማይመጣጠኑ ታስረዳለች።

“በጨርቅ ምርት ከተሰማሩ ትልልቅ ፋብሪካዎች በተጨማሪ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ እንደኛ አይነት ዲዛይነሮችም ማስክ ማምረት አለባቸው” ትላለች።

አያይዛም “አሁን ሌላ ሥራ፣ የገቢ ምንጭም ስለሌለ ሁሉም ተረባርቦ ማስክ፣ ጋውንና ለህክምና የሚውሉ የጨርቅ ውጤቶችን በመሥራት ኮሮናቫይረስን መታገል አለብን። ሠራተኞች ሥራ ላይ እንዲቆዩ ያስችላል” ስትል ትናገራለች።

ቤቱ የስፌት ማሽን ያለው ሰው ለቤተሰቦቹ ወይም ለጓደኞቹ ማስክ እንዲሠራም ዲዛይነሯ ትመክራለች።

በቤት ስለሚዘጋጅ ጭምብል ማወቅ ያለብዎ. . .

• ጭንብሉ አፍና አፍንጫዎን በአግባቡ መሸፈን አለበት። ፊትዎ ላይ እንዲቀመጥ ጆሮዎ ላይ የሚታሰር ገመድ ሊዘጋጅለትም ይገባል።

• ከጥጥ ወይም ከሐር የተሠሩ ጨርቆች ማስክ ለመሥራት ተመራጭ እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። እነዚህን ማግኘት ካልቻሉ ግን ቤት ውስጥ ባለ ጨርቅ ለማዘጋጀት ይሞክሩ።

• ጭንብል ከማጥለቅዎም ሆነ ከማውለቅዎ በፊት እጅዎን በሳሙና ሙልጭ አድርገው መታጠብ አለብዎት።

• ማስክ በማይጠቀሙበት ወቅት ላስቲክ ውስጥ ያስቀምጡት፣ አዘውትረው ማጠብም ይጠበቅብዎታል።

• ጭምብል አጥልቀዋል ማለት ከበሽታው ራስን ለመከላከል መወሰድ የሚገባቸው ሌሎች ጥንቃቄዎችን መተው አለብዎ ማለት አይደለም። ጭምብል ቢያደርጉም እንኳን እጅዎን ቢያንስ ለ20 ሰከንድ መታጠብ የግድ ነው።

• አሁን ላይ የፋሽን ዲዛይነሮችን ምሳሌ በማድረግ ጭምብል የሚሠራባቸውን መንገዶች የሚጠቁሙ ብዙ ገፆች አሉ። ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያገኟቸዋል።

• ከአንድ በላይ ማስክ ማዘጋጀት አይዘንጉ! አንዱ እስኪታጠብ ሌላውን ማድረግ ይችላሉ።

• ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ወይም በትክክል የአፍና አፍንጫ ጭምብል ማጥለቅ የማይችሉ ግለሰቦች ጭምብል እንዲጠቀሙ አይመከርም።

ኮሮና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *