ትግራይ
News

“ትግራይ ላይ ያለው ጥላቻ ይስተካከል፤ ካልሆነ ትግራይ ራስዋን የቻለች አገር ናት ብላችሁ አውጁ” ዶ/ር ደብረፅዮን

”በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ጣልቃ ገብነት እንዲሁም በትግራይ ላይ ያለው ጥላቻ የማይስተካከል ከሆነ ትግራይ ራስዋን የቻለች አገር ናት ብላችሁ ልታውጁ ይገባል” ሲሉ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል መልዕክት አስተላለፉ።

ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት ህወሓት የተመሰረተበትን 45ኛውን ዓመት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በመቀሌ ስታዲየም ለታደሙ ሰዎች ባደረጉት ንግግር ነው።

የትግራይ ምክትል ፕሬዝደንት ደብረፅዮን (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፤ “የስልጣን ጊዜያችሁ [የአባልነት ጊዜ] እያለቀ ስለሚገኝ ከመበታተናችሁ በፊት ታሪክ ስሩ። በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ጣልቃ ገብነት፣ በተለይም ትግራይን በተመለከተ በመሪዎች ደረጃ የተሰጡት የጥላቻና የፀረ ህዝብ ንግግሮችን በይፋ ኮንኑ” ብለዋል።

አክለውም “ይህ የማይሆን ከሆነ ትግራይ ራሷን የቻለች አገር መሆኗን ወስኑ፤ አውጁ” ብለዋል።

“አገር በመበተን ሂደት ነበሩ ተብላችሁ በታሪክ እንዳትወቀሱ፤ ግዳጃችሁን ተወጡም” በማለት መልዕክታቸውን በተሰበሰው ህዝብ ፊት አስተላልፈዋል።

ደብረፅዮን (ዶ/ር) ከዚህም በተጨማሪ በትግራይና በኤርትራ መካከል ያለውን ታሪካዊ ዳራም እንዲሁም አሁንም ስላለው ግንኙነት ምክር አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ህወሓት በትጥቅ ትግል በነበረበት ወቅት “የደርግን ስርዓት ለመጣል የትግራይ እና የኤርትራ ልጆች አንድ ጉድጓድ ላይ ተቀብረዋል” ያሉት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ ከኤርትራ ነጻነት በኋላም ቢሆን የትግራይ ህዝብ እና ህወሓት በኤርትራ ህዝብ የነጻነት ጥያቄ የማያወላዳ አቋም በመያዛቸው ብዙ ፖለቲካዊ ተቃውሞ ቢገጥመውም ከአቋሙ ውልፍት እንዳላለ ተናግረዋል።

በሁለቱ ሃገራት ከተካሄደው ጦርነት በኋላ ሰላም ከመምጣቱ በፊትም የኤርትራ ተፈናቃዮችን “አቅፎ ጥላ በመሆን” ለኤርትራ ህዝብ ወዳጅ መሆኑን አስመሰክረዋል ብለዋል።

በየካቲት 11 በዓል ደግሞ የነበሩ ቅራኔዎችን ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ደብረፅዮን (ዶ/ር) የህዝብን ቀጣይነት አስምረውታል።

“መንግሥታት ፈራሾች ናቸው እና ሰላማችንን ለማስቀጠል በህዝቦች መካከል ውይይት እንዲጀመር እንፈልጋለን።” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በትግራይና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ያለውን የቋንቋ እና ባህል ተመሳሳይነት፣ የጋራ ታሪክ እንዲሁም በደም የተሳሰሩ ከመሆናቸው አንፃር ለጦርነት የሚፈላለጉ ህዝቦች አለመሆናቸውን አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።

ለዚህም የተለያዩ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትን በወነጀሉበት ንግግራቸው ህዝቡን የፖለቲካ አጀንዳ መደበቂያ አድርገውታልም ብለዋል።

“የትግራይ እና ኤርትራ ህዝቦችን ወደ ጦርነት ሊማግዱት የሚያስቡ ኃይሎች አሉ፤ የተጀመረውን የሰላም ሂደት ተቋማዊ በሆነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ለፖለቲካ አጀንዳ መደበቅያ እያደረጉት ይገኛሉ” ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ እህትማማች ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ጋር ግጭት የመግባት ምንም አይነት አላማ የለውም የሚሉት ደብረፅዮን (ዶ/ር) ሁለቱን ሃገራት ወደ ጦርነት ለመክተት የሚደረጉ ሴራዎች እንዳሉም አልደበቁም።

ሁለቱን ሃገራት የሚያገናኙ መንገዶች መዘጋት እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራውያን የስደተኞች መጠለያ እንዲዘጉ እና አዳዲስ ስደተኞች እንዳይቀበሉ የማድረግ ሥራ “በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥት የተደረገ ሴራ ነው” ብለዋል።

አክለውም “የኤርትራ ህዝብ ችግር ችግራችን ስለሆነ ለእናንተ የሚዘጋ በር የለንም። ትግራይ አገራችሁ ነው፤ የኤርትራ ሠራዊት ትግራይ አገርህ ነው። እየታለመ ያለው የፖለቲካ ሴራ አብረን እናክሽፈው” በማለት ንግግራቸውን አድርገዋል።

በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ስላለው የሠራዊት ስምሪት እና እሱን ተከትሎ ስለተከሰተው ጉዳት ተጠያቂ ሊኖር ይገባል ያሉት ደብረፅዮን (ዶ/ር)፤ ስለየትኛው የሠራዊት ስምሪት እና ጉዳት እንደሆነ ያሉት ነገር የለም።

ምንጭ፨ ቢቢሲ  የአማርኛ ክፍል

 

Ethiopia: The challenge to the TPLF…from Tigray’s own grassroots

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *