abiy
News

“እኛ በህይወት እያለን የኢትዮጵያን መፍረስ አንፈቅድም” ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከእንደራሴዎ ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖችን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በክልሉ የአደረጃጀት ጉዳይን በሚመለከት ያሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥናቶች መደረጋቸውን በማንሳት አሁን ግን ጉዳዩ ተጠናቆ ፌዴሬሸን ምክር ቤት እጅ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።

“ከአሁን በኋላ ጉዳዩ የሚመለከተው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው” ካሉ በኋላ በአንዳንድ ዞኖች በመንግሥት ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ማስቸገራቸውን ገልፀዋል።

“እዚህም እዚያም መጉረስ የሚፈልጉ” ያሏቸው እነነዚህ ግለሰቦች በመንግሥት መኪና [ኮብራ] ተቀምጠው ክልሉን የሚያተራምሱ አሉ በማለት አስተጠንቅቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ስለህዳሴ ግድብ በሰጡት ማብራሪያ ግድቡ ግንባታው ተጠናቅቆ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር ተናግረው በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ወደኋላ እንደማይመለስ አረጋግጠዋል።

አርቲስ ሃጫሉ ሁንዴሳ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱ ሲቀጠፍ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የአባይን ጉዳይ እያየ እንደነበር አስታውሰዋል።

ድምጻዊ ሃጫሉን “ጀግናና ቆራጥ ታጋይ ነበር” ሲሉም አሞካሽተውታል።

ከሃጫሉ ግድያ በኋላ የሚነሱ በተለያዩ ዜናዎች የሚፈለገው “የኢትዮጵያ መንግሥት ዓይኑን ከህዳሴ ግድቡ ላይ እንዲያነሳ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

“ሰበር ዜናዎች እንሰማለን፣ ቋሚ ሰበር ዜናችን ግን አገራዊ ትልማችንን ማሳካት ነው” በማለት ከዚያ ላይ ዓይናችንን አናነሳም ብለዋል።

አዳዲስ ጉዳዮችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያመጡ ላሉ አካላት በማለት “አገር አፍርሶ፣ ብሔርን ከብሔር አባልቶ መንግሥት መሆን አይቻልም” ሲሉም ተናግረዋል።

እያባሉ መንግሥት መሆን አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሰው በግፍ እየገደሉ እና ንብረት እያወደሙ አገር መምራት አይቻልም ቁስሉም በአንድ ቀን አይሽርም ሲሉ አስረድተዋል።

“ለጉርሻ ስንጣላ ሌላው መሶቡ እንዳይሰረቅብን” በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነትና የሚያስፈልገውን ጥንቃቄ ገልፀዋል።

አሁንም በግራ በቀኝ ሰው ለመግደልና ለሽብር የምትዘጋጁ በማለትም ቆም ብለው እንዲያስቡ አስጠንቅቀዋል።

“እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ የሚሞት ይሞታል እንጂ የጀመርነው አይቆምም” በማለት መንግሥት የጀመራቸው የልማት ሥራዎችን እንደሚያስቀጥል አብራርተዋል።

ከአገር ውጪ በመሆን በአገር ውስጥ ተቃውሞ እንዲካሄድ ለሚቀሰቅሱ ሰዎች ደግሞ “ከአገር ውጪ ሆኖ ተነስ ተቀመጥ ማለት ድል አምጥቶ አያውቅም ወደፊትም አያመጣም” በማለት በተለይ የሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ አመጽ መቀጠል አለበት ለሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች “ቢያንስ ቢያንስ የሃጫሉን መንገድ መከተል አለባችሁ” ብለዋል።

ይህ ሥርዓት ነው ያልተመቸን የሚል አካል የውጊያ መድረኩ እዚህ ስለሆነ እዚህ መጥቶ የሚያሰልፈው ኃይል ፊት ለፊት ሆኖ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም አብራርተዋል።

“መቀመጫውን እያፈረሰ ለአገረ እታገላለሁ ማለት ሞኝነት ነው” በማለትም የኦሮሞ ሕዝብ የትጥቅ ትግል ያስፈልገዋል ብዬ አላምንም ሲሉም አክለዋል።

ዐብይ ኦሮሞ አይደለም የሚል ፖለቲካ በማለት ሲያብራሩም “የእኔን ኦሮሞነት ሰው የሚሰጥ የሚከለክለኝ አይደለም፤. . . ለኦሮሞ የማይጠቅም ዐብይ፣ ለአማራም አይጠቅምም፤ ለወላይታም አይጠቅም፤…. ” ብለዋል።

“የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ እንዲሆን፣ እኩል እንዲሆን አምኜ ታግያለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ሌሎቹን እንዲጨቁን አስቤ አላውቅም ካሉ በኋላ “አሁን ያለው አካሄድ የኦሮሞን ድል ወደኋላ መመለስ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

“ማንም ሰው ኢትዮጵያን እንዲያፈርስ እኛ እያለን አንፈቅድም፤ ማንም ሰው ከኢትዮጵያ በታች ነው” ብለዋል።

መንግሥትን መስደብና መንቀፍ አስጠይቆ አያውቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስድድብ ምነክንያት ዲሞክራሲን ወደ ኋላ አንመልስም በሚል መንግሥታቸው ዝም ብሎ መቆየቱን አስረድተዋል።

“አሁን በአገር ተመጣ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚቻለው መጀመሪያ እኛን ካፈረስክ በኋላ ነው” “በማለት እኛ ተቀምጠን ኢትዮጵያን ማፍረስ የማይፈቀድ መሆኑን በደንብ መገንዘብ ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

“ኦሮሞን የሚከፋፍል ፖለቲካ፤ ኢትዮጵያን የሚከፋፍል ፖለቲካ አይጠቅምም። ኦሮሞ አንድ ነው ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድሞቹ ጋር ኢትዮጵያን ይገነባል” ብለዋል።

እኛ በህይወት እያለን የኢትዮጵያን መፍረስ አንፈቅድም ካሉ በኋላ “ማንም ሰው ከኢትዮጵያ በታች ነው” ብለዋል።

Source: BBC.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *