የወረቀት የብር ኖቶች በኢትዮጵያ
News

ኢትዮጵያ፡ ከ3.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የብር ኖቶች ምን ይዘዋል?

የወረቀት የብር ኖቶች በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ በኋላ አገሪቱ ለ7ኛ ጊዜ የብር ኖቶች ለውጥ ማድረጓን መስከረም 04/2013 ዓ.ም ይፋ ተደርጓል።

በብዙዎች ዘንድ የባንክ ኖቶች ለውጥ ሊኖር ይችላል የሚለው ግምት መነገር ከጀመረ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። አሁን ግን አዲሱ ዓመት በገባ በአራተኛው ቀን ምንም ነገር ሳይሰማ ይፋ የተደረገው የብር ለውጥ አገሪቱ እያካሄደችው ካለው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ እርምጃዎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብር በዘመናት ሂደት ውስጥ በርካታ ለውጦችን ያስተናገደ ሲሆን፤ ከዋጋ አንጻርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

https://youtube.com/watch?v=267t-ZIqoSU

 

ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና የሐሰተኛ የብር ኖት በገበያው ውስጥ በተደጋጋሚ መከሰታቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲዘገብ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የብር ለውጡ ለሕገ ወጥ ተግባራት የሚውለውን ገንዘብ ለማስቀረት፣ ሙስናንና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ይረዳል ብለዋል።

new birr notes

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በአገሪቱ ያጋጠመውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማስተካከል ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ጥረቶች በመደረጋቸው ምጣኔ ሀብቱ ከነበረበት ችግር በመውጣት በማንሰራራት ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

ጨምረውም በአገሪቱ ያለውን የዋጋ ንረት የመቆጣጠሩ ተግባር በሚፈለገው መጠን ማከናወን እንዳልተቻለ ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀስ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መኖሩ ደግሞ ችግሩን በማባባሱ የብር ኖት መቀየር አንድ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል።

ምን ተለወጠ?

አዲሶቹ የብር ኖቶች ቀደም ሲል ከነበሩት በተሻለ ለአጠቃቀም ምቹና ረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ ተደርገው መሰራታቸ የተገለጸ ሲሆን፤ ኖቶቹን በመቀየሩ ሥራ ለህትመት ብቻ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገ ተነግሯል።

ከቀለም አንጻር አዲሱ ባለ 200 ብር ኖት ሐምራዊ፣ ባለ100 ብር ኖት ውሃ ሰማያዊ፣ ባለ50 ብር ኖት ቀይ ብርቱካናማ፣ ባለ10 ብር ኖት ደግሞ አረንጓዴ ቀለም አላቸው።

ቀደም ሲል በዝውውር ውስጥ የቆየው የባለ5 ብር ኖት ለውጥ ሳይደረግበት በሥራ ላይ የሚቆይ ሲሆን፤ ነገር ግን የወረቀት ገንዘቡ ቀስ በቀስ በሳንቲም እንደሚተካ ተገልጿል።

በአዳዲሶቹ የብር ኖቶች ላይ ቀደም ሲል በነበሩት ላይ ያልነበሩ የአገሪቱን ገጽታ የሚያሳዩ ምስሎች የተካተቱበት ሲሆን፤ በዚህም በባለ አስር ብር ኖት ላይ ግመል፣ በባለ መቶ ብር ኖት ላይ ደግሞ የሶፍ ኡመር ዋሻና የሐረር ግንብ እንዲካተቱባቸው ተደርጓል።

ከባንክ ውጪ ያለ ብር

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ እንዳመለከቱት “ከኢትዮጵያ ውጪ በጎረቤት አገራት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያ ብር ተከማችቶ ይገኛል።”

ከብር ለውጡ ጋር ተያይዞም በውጪ አገራት ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብር ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ብሔራዊ ባንክ ያወጣው ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ በቤት ውስጥ ማስቀመጥ የሚከለክለው ሕግም ተግባራዊ መሆኑ የሚቀጥል ሲሆን፤ ይህንን ደንብ በመተላለፍ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ በቁጥጥር ስር ውሎ ለመንግሥት አገልግሎት ይውላል። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በየጊዜው ድንገተኛ ፍተሻ እንደሚኖርም ተገልጿል።

የብር ለውጥ ሂደት

ላለፉት 23 ዓመታት በዝውውር ላይ የነበሩትን የብር ኖቶች ከገበያ በማስወጣት በአዲሶቹ የመተካቱ ሂደት በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጧል።

ነገር ግን አሮጌዎቹን የብር ኖቶች በአዲስ በመተካቱ ሂደት ውስጥ 100 ሺህ እና ከዚያ በላይ ብር ያላቸው ሰዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መቀየር እንዳለባቸው ተገልጿል።

በዚህ ሂደት ውስጥ እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ ለሚደረግ የብር ለውጥ ቀጥታ ገንዘቡን በመስጠት የሚከናወን ሲሆን፤ ከአስር ሺህ ብር በላይ የሚቀየር ከሆነ ደግሞ ብሩን ለመለወጥ ባመጣው ግለሰብ ስም የባንክ ደብተር ተከፍቶ እንዲቀመጥ ይደረጋል ተብሏል።

የደኅንነት ገጽታዎች

ይፋ የተደረጉት አዳዲሶቹ የብር ኖቶች አስመስለው የሚሰሩ ሐሰተኛ የብር ኖቶችን ለመከላከልና ለመለየት በሚያስችል ሁኔታ የተለያዩ የደኅንነት መጠበቂያ ገጽታዎች እንዲኖሯቸው ተደርጓል።

በተጨማሪም ለዓይነ ስውራን አጠቃቀም እንዲያመች የመለያ ምልክት ያለው ሲሆን፤ በዚህም ዓይነ ስውራን የብሩን ዋጋ በእጅ ዳሰሳ ማወቅ የሚችሉበት ምልክትና የደኅንነት መጠበቂያ ገጽታ አላቸው።

ከዚህ ባሻገርም የብር ኖቱ ወደ ላይ ወይም ወደታች በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ደማቅ የቀለም ፍንጣቂ የደኅንነት መጠበቂያ ገጽታ ያለው ሲሆን፤ የብር ኖቶቱ በእጅ ሲዳሰሱ የመጎርበጥ ስሜት እንዲሁም የብሩ ዋጋ ይታያል።

አዲሶቹ ኖቶች ተጨማሪ ባለቀለም ኮከብ የደኅንነት ገጽታን ከማካተታቸው ባሻገር አብረቅራቂ የደኅንነት መጠበቂያ ክር፤ በክሩ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስያሜ በምህጻረ ቃላት በአማርኛና በእንግሊዝኛ እንዲሁም የብሩ መጠን ሰፍሮ ይገኛል።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲሶቹ የብር ኖቶችን ወደ ብርሃን አቅጣጫ በማዞር ሲታዩ ከፊት ከሚታየው ምስል ትይዩ ተመሳሳይ ደብዛዛ መልክ የያዘ ምልክት ይታያል።

እንዲሁም የብር ኖቶቹ በብርሃን አቅጣጫ ሲታዮ ኳስ የሚመስሉ ምልክቶች ከኖቶቹ በስተጀርባ ካለው ተመሳሳይ ምልክት ጋር በፍፁም ትይዩ ሆነው በአንድ ቦታ ላይ ያርፋሉ።

የብር ለውጥ ታሪክ በኢትዮጵያ

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙት የብር ኖቶች ወደ ዝውውር እንዲገቡ የተደረጉት ከ23 ዓመት በፊት በ1990 ዓ.ም ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ እንደነበረ ይታወሳል።

ከአጼ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ በነበሩ የገንዘብ የወረቀት ገንዘቦች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ለውጥ የተደረገ ሲሆን፤ ወደ አምሳ ዓመታት በሚጠጋው የንጉሡ የሥልጣን ዘመን አራት ጊዜ የብር ኖቶች ለውጥ ተደርጓል።

ወታደራዊው መንግሥት ዘውዳዊውን ሥርዓት አስወግዶ አገሪቱን መምራት ከጀመረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በ1969 ዓ.ም የንጉሡ ምስልን የያዙትን የመገበያያ ገንዘቦች ለውጦት ቆይቷል።

በተመሳሳይም ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላም ለሰባት ዓመታት ያህል ቀድሞ የነበረውን ገንዘብ ሲጠቀም ቆይቶ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የድንበር ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ የብር ኖቶቹ እንዲቀየሩ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ አገልግሎት ላይ የነበሩት የገንዘብ ኖቶች 1፣ 5፣ 10፣ 50 እና 100 ብር የነበሩ ሲሆን፤ ለረጀም ጊዜ ከፍተኛ ዋጋ ያለው የገንዘብ ኖት 100 ብር ሆኖ ቆይቷል።

ቢሆንም ግን በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ ከዋሉት የብር ኖቶች መካከል የ2 ብር እና የ500 ብር ኖቶች ነበሩበት።

ስለዚህም በአገሪቱ የወረቀት ገንዘብ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ የነበረው የብር ኖት ባለ 500 ብር ኖት የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ግን ከግብይት እንዲወጣ መደረጉን የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል።

ስለዚህም አሁን ከወረቀት የብር ኖቶች መካከል እንዲገባ የተደረገው የባለ 200 ብር ኖት በታሪክ ሁለተኛው ከፍተኛ ዋጋ ያለው ሲሆን ወደገበያ ሲገባም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የብር ኖት ለውጥ እንደሚደረግ በተለያዩ መንገዶች ሲነገር የቆየ ሲሆን፤ ከብር ዋጋ መቀነስ ጋር ተያይዞ 500 ዋጋ ያለው የብር ኖት ወደ ገበያ እንደሚገባ አንዳንድ ሰዎች ሲገልጹ ቆይተው ነበር።

በአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች መደረግ ከጀመሩባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንደሚካሄድ በጉምሩክና በፖሊስ በኩል በተደጋጋሚ የሚወጡ ሪፖርቶች የሚያመለክቱ ሲሆን፤ ይህም ለውጥ ያስፈለገው ይህንኑ ለመከላከል መሆኑ ተነግሯል።

Source: bbc.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *