Socepp-Canada
Analysis

የሽግግር  ፍትህ  ሁሉንም ያጠቃል

በመንግስትና በህወሀት መሀል በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት እንደተደረሰ በኖቨምበር 2 ፣ 2022  በቀረበው ይፋ  መግለጫ  ውስጥ የሽግግር ወቅት የፍትህ ሂደት እውን አንደሚደረግ  ስምምነት መደረሱ ተጠቅሷል።

ይህንኑ የመንግስት ዋናው ተደራዳሪ  አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ዛሬ አጉልተው አቅርበውታል፡፡ ይህ መልካም ቢሆንም  ውጤታማ እንዲሆን  ሰፋ አድርጎ መመልከት ይጠይቃል፡፡

በሀገራችን የተፈጸመው  በመላው የስው ልጅ ላይ የተፈጸመ ወንጀልነት  እስከ  የዘር ማጥፋት  ሊታይ የሚችሉ  የመብት ረገጣ  ባለፉት አራት አመታት ብቻ  ሳይሆን ቢያንስ የ30 አመታት እድሜን ያቆጠረ ነው፡፡

ይህ ደግሞ በብዙ መረጃዎች የተደገፈ ራሱ መንግስትም ያመነው ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ባለፈችው ሀገራችን ውስጥ የሽግግር ፍትህን እውን እናደርጋለን ከተባለ ይህም ሰፊ የህዝብ ተቀባይነት እንዲኖረውና ትክክለኛ ማህበራዊ ፈውስን ለማስገኘት እንዲችል ሰፊ  ጠለቅ ያለና  ቢያንስም ላለፉት 30 አመታት የተፈጸመውን ያልተዘጋ አጀንዳ የሚመለከት ሊሆን ይገባል፡፡

ከዚህ ውጭ የሚሆን የሽግግር ፍትህ ሂደት ሀወሀት አዲስ አባባን ሲቆጣጠር እንዳደረገው ጎደሎ የሽግግር ፍትህ ብቻ  ሳይሆን ፍትሀዊነትም ይጎድለዋል፡፡

የሽግግር ፍትህ በአንዱ የማሀበረስብ ክፍል ላይ የደረስው ጉዳት ቦታ የሚሰጠው ሊላው ተሸፋፍኖ የሚያልፍ ሲሆን መሰረታዊ የፍትህ መዛባት ይከሰታል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ሁለት አመት የተፈጸመ ጭፍጭፋ ይመረመራል ይህንንም የፈጸሙ ለፍርድ ይቀርባሉ  ሲባል፣ በጋምቤላ ፣ በ አዲስ አበባ፣ በጎንደር እየሱስ ቤተ ክርስቲያን፣ በአዋሳ ፣በቢሸፍቱ፣ በወለጋ፣ በደብረብርሀን በአምቦ  በቴፒ ወዘተ የተፈጸመው ጭፍጨፋ የማይመረመርበት ወንጀለኞቹም ለፍርድ የማይቀርቡበት ምን ምክንያት አለ?  ባለፉት ሁለት አመታት የተሰወሩ ግልስቦችን ጉዳይ እንመረምራለን ሲባል፣ በመንግስታ የጸጥታ ሀይሎች ታፍነው ላለፉት ሰላሳ አመታት  መዳረሻቸው ያልታወቀውን የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ  የማይታይበት ምን ፍትሀዊ ምክንያት ይኖራል?

ይህ አሁን መንግስትና ህወሀት የደረሱበት የሽግግር ሂደት ፍትህ ውጤታማ እንዲሆን  አውዱን  ሰፋ አድርጎ የሚጓዝበትን ሂደት  ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  ዋናው ነገር በሀገራችን ውስጥ ቀደም ሲል የተፈጸመውን ጥፋት በአግባቡ ተረድቶና መደምደሚያ እንዲኖረው አድርጎ ሁለተኛ እንዳይደገም ትምህርት ወስዶ ተጎጅዎችም ፍትህን አግኝተው ለመጓዝ ሙሉ ፍላጎትና ቅን መንፈስ የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡

ሁኔታው ውስብስብና አድካሚ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ላይ በጥድፊያ ከመሮጥ ረጋ ብሎ በሰፊው ማሰብ እንዴት ብናስኬደው ሰፊ ውጤትን ያስገኛል ብሎ መመካከር   በቅንነትም ማቀድና፣ መተግበር ያስፈልጋል፡፡የሀገራችን ኢትዮጵያ  ባለደርሻ አካላት መንግስትና ሀወሀት ብቻ እንዳልሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡

ይህ ሳይሆን  ከ30 አመት ውስጥ 2 አመትን ቀንጭቦ ለመመልከት መጣር ጊዜና ጉልበትን ማባከን ብቻ ሳይሆን የተወሰነ አካልን ከነወንጀሉ እንዲቀጥል ማድረግ ሌላውን ደግሞ  የደረስበትን በደል ቦታ አለመስጠት ወይም አሳንሶ ማየት  እንዳይሆን ያሰጋል፡፡

ይህ ታዲያ ፍትህንም ማህበራዊ እርቅንም እውን ሊያደርግ አይችልም፡፡ ቀደም ያሉ ጎደሎ እና በግማሽ ልብ የተካሄዱ የተለያዩ ሙከራዎች ውጤት ገንቢ እንዳልነበረ ለሁልም ግልጥ ነው፡፡ ይህን ስሀተት አሁንም ደግሞ ላለመስራት ገና ከወዲሁ ጥንቃቄ ያሻል፡፡

የኛ ምክር  ፍትህ ለሁሉም  የሽግግር ፍትህን transitional justice እውን ለማድረግም ሁሉም ባለድርሻዎች ከመጀመሪያው ጀምሮ ተሳታፊ ይሁኑ የሚል ነው፡፡

ሰላምና ፍትህ ለሁሉም ኢትዮጰያውያን

 

 

Source: SOCCEP CANANDA

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *