EPRP ESCC NA
Press Release

የኢሕአፓ ሊቀመንበር ረ/ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ መታሠራቸውን አስመልክቶ ከኢሕአፓ የድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሊቀመንበር ረ/ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ መጋቢት ፲፰ ቀን ፪ ሺህ ፲፮ ዓ. ም በድርጅቱ ጽ/ቤት ውስጥ በሥራ ላይ እንዳሉ በህገወጥ መንገድ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ መንግሥት ቀደም ሲል የድርጅታችን ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃምን ሕገ መንገሥቱ በሚፈቅደው መሠረት በሰላማዊ መንገድ “ጦርነት ይቁም፣ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ ቃል ሰላማዊ ሠልፍ እንዲደረግ ከሌሎች ድርጅቶችና አገር ወዳድ ግለሰቦች ጋር በመተባበር በመንቀሳቀሳቸው፣ እሳቸውና የአስተባባሪ ኮሚቴው አባላት ለእሥር ተዳርገዋል፡፡ በአገራችን የዜጎች በሕይወት የመኖር ዋስትና እንዲረጋገጥ፣ ዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን

እንዲሁም የአገራችን ዘርፈ-ብዙ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ፣ ኢሕአፓ ከሌሎች ሰላምና አገር ወዳድ ወገኖች ጋር በመተባበር ጦርነት እንዲቆም፤ ዜጎች ያለፍርድ መታፈናቸው እንዲያበቃ፤ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታፈኑና በየማጎሪያ ካምፑ የታሰሩ እንዲፈቱ በመታገላቸው ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበራችን አራት ወር ለሚጠጋ ጊዜ አዋሽ አርባ ተግዘው ከቆዩ በኋላ ፍርድ ቤት በነፃ ለቋቸዋል፡፡ ይህ በሕገወጥ መንገድ ዜጎችን ማሠርና ማንገላታት የሚያመለክተው ገዥው ፓርቲ እየሄደበት ያለውን አምባገነናዊ የፈላጭ ቆራጭነት ባህሪውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

ኢሕአፓ መሠረታዊ የአገራችን ችግሮች እንዲፈቱ የሚያደርገውን ትግል ለማሰናከልና መሪዎቻችን ይፈቱ በሚል ጥያቄ ዙሪያ እንዲጠመድ የድርጅታችን ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር በተፈቱ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የድርጅቱ ሊቀመንበር በትናንትናው ዕለት በፀጥታ ኃይሎች ታፍነው ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸው ምን ማለት ነው? በሕገ መንግሥቱ በተፈቀደው መሠረት ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር መንቀሳቀሳቸው ጥፋታቸው የት ላይ ነው? በአገራችን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት እንደታየው ንፁሃን ዜጎችን ካሠሩ በኋላ የሃሰት ክሶችን እየፈበረኩ ማንገላታት የታዘብነው ስለሆነ ይህ እኩይ ተግባር ለአንዴና ለሁል ጊዜ ማብቃት አለበት እንላለን፡፡

ረ/ፕሮፌሰር ዝናቡን ለማሠር የተመሠረተ ክስ ወይንም ከፍርድ ቤት የተሰጠ ትዕዛዝ ሳይኖር ወደ እሥር ተወርውረው ላለፉት ሁለት ቀናት በእሥር ላይ መሆናቸውን ከቤተሰቦቻቸው ከተገኘው ዜና ለመረዳት ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በረ/ፕሮፌሰር ዝናቡ ላይ የተፈጸመውን ኢ-ፍትሃዊ አፈናና እስራት በመረዳት በአስቸኳይ እንዲፈቱ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።

በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲም ሆነ ሌላ አንዱ አሳሪ ሌላው ታሳሪ የሚሆንባትን ኢትዮጵያ የኢሕአፓ ደጋፊዎች አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ኢሕአፓ ለዜጎች እኩልነትና ሰላም ይሰፍን ዘንድ የሚታገል ድርጅት ነው። ፍትኅ እንዲሰፍን፣ ሰላምና እኩልነት እንዲኖር፣ መብቶች እንዲከበሩ ለመታገል ሰላማዊ የትግል ስልትን መርጦ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ የሚታገል ድርጅትን መሪ ገዥው ፓርቲ ለሥልጣኔ ያስጋኛል በሚል ፍራቻ የሚያስርና የሚያፍንበት አካሄድ ፍጹም አባገነናዊነት ነው፡፡ ስለሆነም በሥልጣን ላይ ያለው የብልጽግና ፓርቲ በምክክርና በውይይት ከአቻ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመርኅና ሕግን ተንተርሶና አክብሮ የሚሠራ ሳይሆን ከፓርላማ አባላት እስከ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አባላትን ማፈንና ማሠር ኢ-ፍትሃዊ በመሆኑ ድርጊቱን በጥብቅ እንኮንናለን፡፡ ይህ የገዥው ፓርቲ የማናለብኝነት ጉዞም በሕግ እንዲገታ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ዜጎች በዘራቸውና በሃይማኖታቸው ምክንያት በሺዎች እየተፈናቀሉና እየታሠሩ እንዲሁም በጨካኝ ገዳዮች በየመንገዱ እየሞቱ ያለባት አገር ሆናለች። ለአለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክዓምድር ላይ የቆየው ኢሕአፓ ለዘመናት የታገለለትንና አያሌ ሰማዕታትን የገበረበትን የሕግ የበላይነት፣ የሕዝብ ሰላምና መብት መከበርን አሁንም ከፍ አርጎ ትግሉን በሰላማዊው መድረክ ይቀጥላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም በአምባገነኖች እንዳይገዛ ማንኛውንም ጭቆና፣ አፈናና ሕገወጥ መንግሥታዊ አካሄድን በዝምታ እንዳይቀበል ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በመጨረሻም የድርጅታችን ሊቀመንበር ረ/ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከታገቱበት በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ እንዲሁም በአዋሽ አርባና በተለያዩ የማጎሪያ ቦታዎች የታገቱና ለፍርድ ያልቀረቡ ዜጎች ሁሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡

ዜጎችን ማፈን፣ ማንገላታትና ማሠር ይቁም!

መጋቢት ፲፱ ቀን ፪ ሺህ ፲፮ ዓ. ም

March 28, 2024

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *