Analysis

ኢትዮጵያ፡ እንደገና ሰው እንድንሆን፣ እንደገና አገር እንዲኖረን፣ እንደገና መንግሥት እንዲኖረን … በአንዱ ዓለም ተፈራ

አንዱ ዓለም ተፈራ:-

ሐሙስ፣ የካቲት ፲ ፫ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፯ ዓ. ም.

ውድ አንባቢ፤

ከ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓ. ም. ጀምሮ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደረሰብን በደል፣ በንብረታችን ላይ የተካሄደው ውድመት፣ በአስተሳሰባችን ውስጥ የሰረጸው አለመተማመን፣ በያንዳንዱ ቤተሰብ ዘንድ የደረሰው መከፋፈልና መበታተን፣ የፍርሃት መንገሥ፣ የተሰፋ ማጣት፣ በገፍ የመሰደድ፣ ሌላም ሌላም ተደምሮ፤ እንደ ሕዝብ ያሳለፍናቸው ሃምሳ ዓመታት፤ ትክክል የሰው ኑሮ ነበር ማለት አይቻልም። በደርግ ጊዜ፤ አረመኔነት ነገሠ። ግድያ የፖለቲካ መስመር ማስፈጸሚያ መገልገያ ሆነ። ሬሳ በመንገድ ተጥሎ ውሎ አደረ። ቀጥሎ በ “ትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ጊዜ፤ ክልል የሚባሉ ትልልቅ አጥሮች በመካከላችን ተገንብተው፤ መከፋፈል፣ አለመግባባት፣ መጠላላት፣ መበላላት ነገሠ። አሁን ተረኛ ሆኖ በነገሠው የአክራሪ ኦሮሞ ገዥ ቡድን፤ የነበረው ከመቀጠሉ በላይ፤ ሥር የሰደደ የመጠፋፋት ሂደቱ፤ በብዙ እጥፍ ተዳምሮ፤ የሟችን ቁጥር እንደ አሸዋ አብዝቶታል። “ዐማራን አጥፍተን ኢትዮጵያዊነትን እናጠፋለን!” በሚል የጥላቻ ፖለቲካ እሳቤ፤ ዐማራ በሚኖርበት በመላ የአገራችን መሬት፤ እንዲጠፋ ተዘምቶበታል። በዚህ የሁሉን ላጥፋ መንገድ፤ የት ልንደርስ ነው? ከዚህ ወጥተን፣ እንደገና ሰው እንድሆን፣ እንደገና የአገር ባለቤት እንድንሆን፣ እንደገና መንግሥት እንድንገነባ፤ ምንድን ነው ከዚህ እውነታ ወጥተን፤ በአካል ብቻ ሳይሆን፤ በአስተሳሰባችንም ሰው ሆነን፤ ወደፊት ለሚመጡትም ሰው መሆንን አውርሰን ለማለፍ፤ ሊፈውሰን የሚችለው? የምለውን እሄድበታለሁ።

አሁን ካለንበት ተጨባጩና ሃሳባዊ ነበሬታ እንድንወጣ፤ የግድ የሽግግር ወቅት ያስፈልገናል። በርግጥ ይሄን ለማስብም ትንፋሽ እንድናገኝ፤ መጀመሪያ አሁን ያለው ገዢ ቡድን ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ መወገድ አለበት። ይሄ ደግሞ፤ በልመና፣ በጸሎት፣ በመለማመጥ የሚደረስበት እውነታ ሳይሆን፤ ሕዝቡ በክንዱ እንዲሆን የሚያደርገው ሀቅ ነው። ዐማራን ማጥፋት ዘመቻው ባስቸኳይ መቆም አለበት። ከዐማራው ውጪም ሰላም አለ ብሎ ማለት፤ የዋህነት ነው። የአምባገነን ስነ ባህርይ፤ ማንንም አለማመን፣ ሁሉንም በቁጥጥሩ ሥር የማድረግ፣ ተከታይ አለማፍራት፣ በእምነቱም በሱ ጭንቅላት ካለው የተሸዋወረ ዓለም ውጪ ምንም ነገር የለም! ብሎ መካድ ናቸው። ስለዚህ፤ የአክራሪው ኦሮሞ ገዢ ቡድን በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ፤ ሰላም፣ ልማት፣ አብሮ መሥራት፤ የወደፊትና ተከታይ ማፍራት የሚባል አይታሰብም። የዐማራ ህልውናም ሆነ የኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል፤ ከሕልውናው ጋር አብረው የሚሄዱ ዕሴቶች አይደሉም።

ሰው ሆነን፣ መልሰን እንደ ሕዝብ፣ አገር ኖሮን እንድንቀጥል፤ በሕዝብ ቁጥጥር ሥር የሆነ፤ አንድ የመታደሻ ሸንጎ ያስፈልገናል። የቀይ ሽብር ግፍና ሰቆቃ መመርመር አለበት። የዘር ክፍፍሉ መጠናትና፤ ጉዳቱና ጥቅሙ መመዘን አለበት። የነፃ አውጪ ግንባሮች መፈልፈልና ውጤታቸውና መዳረሻቸው መጠናት አለበት። ባለፈው ሃምሳ ዓመታት የጠፉ፣ የተሰደዱ፣ የተገደሉ በሙሉ ዝርዝራቸው ተጽፎ፣ በስብስብ፤ “ወደፊት እንዳይደገም!” በሚል አገራዊ እሳቤ፤ መማሪያ እንዲሆን፤ ባንድነት ልንዘግበው ይገባል። እያንዳንዱ የመጣ የሄደ መሪ፤ መፈተሽ አለበት። ይሄ፤ ተከታዩ ገዢ ቡድን፣ ያለፈውን የሚያወግዝበትና የራሱን መላዕክትነት የሚያውጅበት፤ አይደለም። አልፎ ተርፎም፤ ቢቻል ከፋሺስቱ ወረራ ወዲህ ያለው ታሪካችን፤ በትክክል ተመርምሮና ተዘግቦ፤ ለወደፊቱ መማሪያ እንዲሆን፤ በጎና በጎ ያልሆኑ ጎኖች መጠናት አለባቸው። ከዚያ በኋላ ነው፤ “እንደገና ሰው ሆነናል!” ብለን መተንፈስ የምንችለው።

ቅደም ተከተሉን ላስቀምጥ። መጀመሪያ አሁን የዐማራውን የህልውና ትግል እየመሩ ያሉት አርበኞቻችን የፋኖ ታጋዮች ለድል ይብቁ። ይህ በማንኛውም እየተነፈሰ ያለ ሰው ሊደግፈው የሚገባ፤ ልዑል ተግባር ነው። በምንችለው ሁሉ ድጋፍ እናድርግ። ቀጥሎ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ኢትዮጵያዊያን፤ “ነግ በኔ!” ብለው የተነሱትን በማበረታታ፤ ያልተነሱትን እንዲነሱ በመቀስቀስ አገር አቀፍ እንቅስቃሴ እንዲደረግ እንጣር። ከዚያ የሽግግር መንግሥቱ ደረጃ እንደርሳለን። ያን ጊዜ ነው የመታደሻ ሸንጎው የሚመጣው። ይሄ እሳቤ ቀደም ብሎ ነው መደረግ ያለበት። እናም አሁንም ጊዜውን እንጠቀምበትና፤ በያለንበት ይሄን ሀቅ ለማድረግ እንሯሯጥ። ጊዜውን ብንጠቀምበት የኛ እናደርገዋለን።

በሚረባ በማይረባው ልዩነትን ከማራገብ፤ በተቻለ መጠን የጋራ የሆነ ጉዳያችንን በማስቀደም በትብብር ወደፊት ብንሄድ፤ ታሪክ ትውልዳችንን በበጎ ያየዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *