EPRP
Press Release

በወጣቷ ላይ የደረሰው ሰቆቃ በቅርብ ጊዜያት በአገራችን ለተፈጸሙ ግፎች በቂ ማሳያ ነው!

*በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከመኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄና እናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ*

ከምትማርበት ዩኒቨርስቲ ከዓመታት በፊት ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር ታፍና ተወስዳ እጅግ አሰቃቂ በደል ከደረሰባቸው አንዷ እንደሆነች የገለጸችው ወጣት ብርትኳን ተመስገን የደረሰባትን ግፍና አኹን እየመራች ያለችውን እጅግ ፈታኝ የሕይወት ውጣ ውረድ የዚህ ዓይነት ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች በማይደፍሩት መልኩ በድፍረት በሚዲያ ቀርባ አስረድታለች።

ይኼ በሕዝባችን ዘንድ በከፍተኛ ኹኔታ ሲጠየቅ የነበረና አንዳች መፍትሔ ሳይሰጠው ይባስ ብሎ በመንግሥት አካላት ዘንድ እጅግ የተጣረሱና የተድበሰበሱ መረጃዎች ሲቀርብበት የኖረ ግፍ ነው።

ብርትኳን ላይ የደረሰው ግፍ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጸሙ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ በደሎች ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ እንጂ ብቸኛው አይደለም። በዚኹ አጋጣሚ የልጅቷ ደህንነት ተጠብቆና መቋቋሚያ አግኝታ ስለሌሎች ደብዛቸው ስለጠፋ ተማሪዎች አንዳች ፍንጭ የሚሰጡ መረጃዎችን ለማገጣጠም መጣር ሲገባ ልጅቷ ጋር ያለውን እውነት ለማዳፈን ሙከራ ማድረግ የግፉ ተባባሪ ከመኾን ተለይቶ አይታይም።

በትብብር የምንሠራ ፓርቲዎች በወጣቷ ጉዳይ የቅርብ ክትትል እንደምናደርግ ቃል እንየገባን ሕዝባችን ችግሮቹ ሥርዓት ወለድ መኾናቸውን በውል ተገንዝቦ እርስ በእርስ ጣት ከመጠቋቆም እንዲወጣና በጋራ እንዲታገል ከከፋው ሰቆቃም በአንድነት እንድንወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

መንግሥት የብርትኳንና መሰል ጓደኞቿን እገታ ቢያንስ ለችግሩ እውቅና ሰጥቶና ሕዝብን አስተባብሮ ወደ መፍትሔው መሔድ ሲገባው ማድበስበስን በመምረጡ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ችግሩ ሥር ሰዶ ከእለት እለት እየከፋ ሄዷል፡፡

መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል እየተጓዘ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ወረ ጃርሶ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ አሊዶሮ በተባለ ቦታ አሽከርካሪውን ጨምሮ መላ ተሳፋሪዎች መታገታቸውንና ለማስለቀቂያ የሚኾን በነፍስ ወከፍ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየተጠየቀባቸው መኾኑን ሰምተናል፡፡

በተመሳሳይ መጋቢት ፲፬ ቀን በዚኹ ሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ጎርፎ ከተማ አካባቢ የታጠቁ ቡድኖች ከቀኑ ፲ ሰዓት ገደማ በኹለት ተሽከርካሪዎች ላይ በፈጸሙት እገታ አርባ ያኽል ሰዎች መታፈናቸውን ሰምተናል፡፡ ለጊዜው ለኹለቱም እገታዎች በይፋ ሓላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም በአካባቢው መሰል ድርጊት ፈጻሚዎች ያለምንም ከልካይ ባሻቸው ወቅትና በተደጋጋሚ ጊዜያት እገታ እየፈጸሙ አሰቃቂ ግድያ የሚፈጸምበትና ብዙ ሚሊዮን ብር ካሳ የሚጠየቅበት መሥመር አካባቢው ደግሞ “የሞት ቀጠና” ከኾነ ውሎ አድሯል፡፡

በተደጋጋሚ እንደገለጽነው መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ የኾነውን የዜጎችን ወጥቶ የመግባት ዋስትና ማስጠበቅ አለመቻል፣ ፍትሕ አለመስፈን በአገር ደረጃ መግደልና ማገት ቀላል እንዲኾን አልፎ ተርፎም ለእነዚኽና መሰል ቡድኖች የገቢ ምንጭ ጭምር ተደርጎ እንዲታይ አድርጎታል፡፡

በትብብር የምንሠራ ፓርቲዎች በእገታው የተሳተፈ የትኛውም ቡድን በንጹሓን ሕይወት መቆመሩን እንዲያቆምና የታገቱ ዜጎች ያለምንም ቅድመ ኹኔታ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄና እናት ፓርቲ

መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *